Amharic Blog

Book a Consultation
100% Secure & Confidential
★★★★★
100+ Reviews

Amharic Blog

የተከበራችሁ ውድ ደምበኞቻችን;

ታህሳስ 20/2021 ዓ.ም የአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆስፍ አር ባይደን እና ምክትል ፕሬዝደንቷ ካማላ ሃሪስ ቃለ መሃላ ፈፅመው የሃገሪቱን ስልጣን ተረክበዋል፡፡ ስልጣን በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ አዲሱ አስተዳደር ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ያቀረቧቸው ረቂቅ ህጎች እንደኛ ላሉ የኢሚግሬሽን ጠበቃዎች መልካም ዜና ያበሰሩ እና ያለፍንባቸውን ተግዳሮቶች የሚያቃልሉ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡

ያለፉት አራት አመታት; በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ ለተሰማራ ባለሙያ በጣም አስቸጋሪ የነበሩ እና የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለሟሟላት ያለመታከት እንድንታገል ያስገደዱን ቢሆንም ያለንን የአመታት የካበተ ልምድ በመጠቀም የእናንተን ጉዳዮች በአግባቡ እና በሚፈለገው መንገድ ዳር ለማድረስ ችለናል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላሳያችሁን ትግስት እና ያላሰለሰ ተስፋ እጅግ እናመሰግናለን፡፡ለራሳችሁ እና ለቤተሰቦቻችሁ የሰነቃችሁትን በዚህች ሃገር ኑሮን የማቃናት ተስፋ አጥብቃችሁ ስለያዛችሁ እና በእምነታችሁ ስለፀናችሁ እናመሰግናለን፡፡

በእርግጥም አንድ አፍሪካ አሜሪካዊ ከሆነ አባት እና እሲያዊ ከሆነች እናት የተወለደች የስደተኞች ልጅ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገሪቱ ቁንጮ ከሆኑ ስልጣኖች አንዱ የሆነውን የምክትል ፕሬዚዳንትነት ስልጣን ስትይዝ :በዚህች ሃገር ማሳካት የሚቻለውን የተስፋ አድማስ ስፋት ይነግረናል፡፡ የካማላ ሃሪስ ታሪክ የሁላችንም ታሪክ ነው፡፡

ከዚህ ስር ጠቅለል ባለ መልኩ አዲሱ አስተዳደር በኤክስኪዩቲቭ አክሽን እና በረቂቅ ህግ መልኩ ያቀረባቸውን በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነጥቦችን ለማስቀመጥ ሞክረናል፡፡ በኤክስኪዩቲቭ አክሽን የቀረቡት ህጎች ተፈፃሚነታቸው ወዲያውኑ ሲሆን በረቂቅ ህግነት የቀረቡት ግን ተፈጻሚ እንዲሆኑ በኮንግረስ ፊት ቀርበው መፅደቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በረቂቅነት የቀረቡትን ህጎችን በማፅደቅ ሂደት ውስጥ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ከባድ ተቃውሞ እንደሚያቀርቡባቸው ይጠበቃል፡፡  ምናልባትም እነዚህ ረቂቅ ህጎች ሙሉ በሙሉ ይፀድቃሉ ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ በረቂቅ ህጉ ውስጥ የተነሱት ሃሳቦች እና በኤክስኪዩቲቭ አክሽን የተወሰኑት ጉዳዮች; አዲሱ አስተዳደር ወደስልጣን በመጣ በጥቂት ቀናት ውስጥ     መነሳታቸው ተስፋ የሚያጭር እና ባለፉት አመታት የነበሩብንን ተግዳሮቶች ለመፍታት ቅድሚያ መሰጠቱን የሚያመላክት ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቀጣይ የምናገኛቸው አዳዲስ መረጃዎች እና ማሻሻያዎች በምን መልኩ ጉዳዮቻችሁን እንደሚመለከቱ ለማወቅ ከቢሯችን ጋር ያላችሁን ግንኙነት በቅርበት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እናሳስባለን፡፡

 

ርዕስ አንድ (1)

በኤክስኪዩቲቭ ኦርደር (በስራ አስፈፃሚው ውሳኔ )የፀደቁ ህጎች

 1. በተወሰኑ የእስልምና እምነት ተከታይ ሃገራት እና የአፍሪካ ሃገራት ላይ ተጥሎ የነበረውን ተጓዥ እገዳ/ገደብ ስለማንሳት       

ጃንዋሪ 20, 2021 ፕሬዚደንት ባይደን ከፈረሟቸው የአስፈጻሚ ውሳኔዎች አንዱ በተወሰኑ የእስልምና እምነት ተከታይ እና የአፍሪካ ሃገራት ላይ ተጥሎ የነበረውን ፍትሃዊ ያልሆነ የተጓዥ እግድ የሚያነሳ ነው፡፡ ይህ እግድ ብዙ ቤተሰቦችን ላለፉት አመታት አለያይቶ የቆየ የቀደመው አስተዳደር ውሳኔ ነበር

በዚህ እግድ መነሳት ምክንያት ከዚህ ቀደም ወደ ዩናይትድ እስቴትስ እንዳይገቡ ተከልክለው የነበሩ እንደ ኢራን፣ሶሪያ፣ የመን የመሳሰሉ የሙስሊም ሃገራት ዜጎችን እና እንደ ናይጄሪያ እና ኤርትራ ያሉ የአፍሪካ ሃገር ዜጎች እግዱ አሁኑኑ ተነስቶላቸዋል፡፡ከዚህም ጋር በተያያዘ የቪዛ ቅድመ ሁኔታ እንዲነሳላቸው አመልክተው ጉዳያቸው እየታየ ያሉ የውጪ ሃገር ዜጎች ቪዛ እንዲሰጣቸው እና እንዲሁም ከዚህ በፊት በነበረው እግድ ምክንያት ማመልከቻቸው ውድቅ የተደረገባቸው ጉዳያቸው በድጋሚ እንዲታይ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ከላይ በተነሱት ሃሳቦች ላይ የሚያተኩር ጉዳይ ያላችሁ ደንበኞቻችን እነዚህ ህጎች ተፈፃሚ ለመሆን የተወሰነ ጊዜ ሊወስድባቸው ስለሚችል ወይም እንደሚችል ስለሚገመት መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች እና አዳዲስ መረጃዎች በቢሯችን ከሚገኙ ጠበቆች ጋር በቅርበት እንድትወያዩ እንመክራለን፡፡

 1. DACA ፕሮግራምን እንደነበር ስለማስቀጠል

ጃንዋሪ 20, 2021 ፕሬዚደንት ባይደን ከፈረሟቸው የአስፈጻሚ ውሳኔዎች መካከል የ ዳካ (DACA) ፕሮግራም በነበረበት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያግዝ ሜሞራንደም አንዱ ነው፡፡ይህ ሜሞራንደም ምንም እንኳን አዲስ አይነት ለውጦችን በፕሮግራሙ ላይ ባይጨምርም ከዚህ በፊት ፕሮግራሙን ለማቋረጥ ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶችን ወደ ጎን በመተው USCIS አዲስ አመልካቾችን መቀበሉን እንዲቀጥል እና የነባር ፍቃድ እድሳት አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያሳስብ ማዘዣ ሆኖ ተፈርሟል፡፡ የ DACA ፕሮግራም በ USCIS የተቀመጡትን መመዘኛዎች ለሚያሟሉ አመልካቾች በየሁለት አመቱ የሚታደስ የስራ ፈቃድ የሚያስገኝ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም ጊዜያዊ የመጓጓዣ ሰነድ (advance parole) ለማግኘት ማመልከቻ ማቅረብ የሚቻልበት ስርአትም ተዘርግቷል፡፡

በቀጣይም ፕሬዚደንት ባይደን የ DACA ስርዓት ተጠቃሚዎች የ ዩናይትድ ሴቴትስ ዜግነት ማግኘት የሚችሉበት መንገድ እንዲፈጠር የሚያግዙ ህጎችን ያካተተ ረቂቅ አዋጅ ለህግ አውጪው ምክር ቤት (ኮንግረስ) ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችን የህግ ቢሯችን በቀጣይ እየተከታተለ የሚያሳውቃችሁ ይሆናል፡፡

 1. የተወሰኑ ከሃገር የማስወጣት ሂደት (Deportation Procedure) ላይ ያሉ ጉዳዮችን 100 ቀናት ስለማዘግየት ወይንም ማዕቀብ ስለማድረግ

ጃንዋሪ 20, 2021 ፕሬዚደንት ባይደን ከፈረሟቸው የአስፈጻሚ ውሳኔዎች እንዱ ከሃገር የማስወጣት ሂደት (deportation procedure) ላይ ያሉ ሰወች ጉዳይን ለ100 ቀናት እንዲዘገይ እና በ ICE እስር ላይ ያሉት ደግሞ ከእስር እንዲፈቱ የሚያዝ ነው፡፡ በዚህ ትዕዛዝ ውስጥ የሚካተቱት ሰዎች በምንም አይነት ከባድ ወንጀል ወይም Aggravated Felony ያልተፈረደባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የላይቤሪያ ተወላጅ ለሆኑ ከአገር የመባረር ዕገዳ ተደርጓል

 1. በመጨረሻም የቀድሞው መሪ በተደጋጋሚ እንደ መፈክር የሚያነሱትን የድንበር ግምብ እንዳይቀጥል አስቁመዋል፡፡

 

ርዕስ ሁለት(2)

የአሜሪካ ግነት ረቂቅ ህግ 2021 (ዩናይትድ ስቴትስ ሲትዝንሺፕ አክት 2021) (በረቂቅ ደረጃ ህግ አውጪው ወይም ንግረስ የቀረቡ ረቂቅ ህጎች)

1/ ጠቅላላ ጉዳዪችን በተመለከተ

1: ከ ታህሳስ 23፣ 2013 (ጃንዋሪ 1, 2021) በፊት በ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአካል የሚገኙ እና ምንም አይነት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ሰዎች ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኝት ማመልከት ይችላሉ፡፡ ይህንንም ፍቃድ ለማግኝት ምንም አይንት አስቸጋሪ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው ወይም ለሃገሪቱ ስጋት የሆነ ጉዳይ ውስጥ የሌሉ እና ግብር ባግባቡ የከፈሉ መሆን ይኖርባቸዋል::

2: በልጅነታቸው ወደ አሜሪካ የመጡ እና የ ዳካ (DACA) ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ፤ እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ እደጋዎች የተነሳ ጌዚያዊ የመቆያ ሰነድ (Temporary Protected Status) ያገኙ እንዲሁም በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ወዲያውኑ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኝት ማመልከት እንደሚችሉ ረቂቁ ህግ ይገልጻል::

3: ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች መኖሪያ ፈቃድ ላገኙ ከሶስት አመታት ብኋላዜግነት ለማግኝት ማመልከቻ ለማስገባት የሚችሉ መሆናቸውን ይገልጻል::

4: በተጨማሪም ከጃኑዋሪ 20, 2017 ብኋላ ከአገር ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሰዎችን በተመለከተ ከመባረራቸው በፊት ለሶስት ዓመታት በአካል አሜሪካን አገር ነዋሪ ክነበሩ በዚህ ህግ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ማለትም ከላይ “በአካል የመገኝት ግዴታዎች” የተባሉት ተፍጻሚ እንዳይሆኑባቸው መጠየቅ የሚችሉ ይሆናል::

5: በአገሪቱ የኢሚግሬሽን ህጎች ላይ የሚገኝው “ኤሊየን”(Alien) የሚለው የሚያንቋሽሽ መጠሪያ ዜጋ ያልሆኑ (noncitizen) በሚል አክባሪ አጠራር እንዲቀየር ይጠይቃል፥፥

6: የዲቪ ሎቶሪ ፕሮግራም እንዲቀጥል፡፡ በተጨማሪም በየአመቱ የሚፈቀደው የቪዛ መጠን ከ55፣000 ወደ 80 ሺህ ከፍ እንዲል፡፡

ማስታወሻ፡- የዲቪ ሎተሪ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚኖር ሰው ጋር ምንም አይነት ዝምድና የሌላቸው ብዙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ዩናይትድ ሴቴትስ ለማምጣት የሚጠቀሙበት መልካም አመራጭ መንገድ ነው፡፡

7: በቀጣይነት ምንም አይነት እምነትን መሰረት ያደረገ የተጓዥ እገዳዎች እንዳይጣሉ መከልከል፡፡

አዲሱ የባይደን አስተዳደር በእስልምና እምነት ተከታይ ሃገራት ላይ ተጥሎ የነበረውን እና ብዙ ደንበኞቻችንን ከቤተሰቦቻቸው አለያይቶ የቆየውን ህግ መሻሩ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላ ማንኛውም ፕሬዝዳንት በአስፈጻሚ ውሳኔዎች ተጠቅሞ ሃይማኖትን ብቻ ተመርኩዞ የሚወጡ ዕገዳዎችን ይከለክላል፡፡

2/ በዝምድና ላይ የተመሰ (Family-based) የኢምግሬሽን ጉዳዮች በተመለከተ የቀረቡ ማሻሻዪች

1: የተከማቹ እና መልስ ያልተሰጠባቸውን ጉዳዮች በፍጥነት መልስ በመስጠት ፣ጉዳዮችን ለማየት ይፍጅ የነበረውን የተራዘመ ጊዜ ማስቀረት ፣ በሀገራት ላይ የተጣሉ የቪዣ መጠን ጣሪያዎችን ከፍ ማድርግ ::

ማስታወሻ:- በዝምድና ላይ የተመሰረቱ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ጥያቄው የሚቀርብለት ዘመድ የሚመጣበት ሃገር ላይ በሚጣሉ የቪዛ መጠን ገደቦች ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ እንደ ሜክሲኮ፣ ህንድ፣ፊሊፒንስ እና ቻይና የመሳሰሉት ሃገሮች በቪዛ መጠን ገደብ የተነሳ በተለየ ረጅም የመጠበቂያ ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡

2: የሶስት አመት እና የ10  አመት ገደቦችን ማስወገድ

ማስታወሻ፡-ይህ ገደብ ብዙዎች በቤተሰብ ወይንም በስራ አማካይነት ቋሚ መኖሪያ ሊያገኙ ሲችሉ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያለህጋዊ ፈቃድ ለስድስት ወራት ወይም ለአንድ አመት ስለቆዩ ብቻ ሶስት ዓመት ወይ አስር አመት ምንም አይነት ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት አይችልም ነበር፡፡

3: በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ከዩናይትድ ስቴትስ ጎን በመቆም በጦርነቱ ለተሳተፉ የፊሊፒንስ ዜጎች እና ለቤተሰቦቻቸው ጥበቃ እንዲደረግ፡፡

4: በዝምድና ላይ የተመሰረተ የኢሚግሬሽን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያገኘ ሰዎች የቪዛ ፕራዮሪቲ ቀን(Visa Priority Date) ከመድረሱ በፊት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በመምጣት መጠበቅ እንዲችሉ፡፡ ይህ ቤተሰቦች ወረፋ እስኪደርሳቸው ተለያይተው የሚጠብቁትን በቤተሰብ ላይ ብዙ ሰቀቀን የሚያመጣውን መለያየት ያስወግዳል፡፡

3/ጥገኝነት እና ሌሎች ሰብአዊ ጥበቃዎችን ላይ ያሉ የኢሚግሬሽን ህጎች

1: ከዚህ በፊት አንድ ግለሰብ ጥገኝነት መጠየቅ የሚችለው በአካል በአሜሪካን ግዛት በገባ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው የሚለው ገደብ እንዲነሳ፡፡

2: የተከማቹ እና መልስ ያልተሰጠባቸውን የጥገኝነት ጥያቄዎች በአስቸኳይ እንዲስተናገዱ አስፈላጊው ገንዘብ (fund) እንዲመደብላቸው፡፡

3: በ U(ዩ) ቪዛ, በ T(ቲ) ቪዛ እንዲሁም VAWA ስር ላሉ ሰዎች ተጨማሪ ጥበቃ እንዲደረግ፡፡  እነኝህ በተለይ ከባድ ወንጀል የተፈጸመባቸው፤ እንዲሁም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የጾታዊ ጥቃት ሰለባዎችን ለመጠበቅ የሚረዳ ህግ ነው፡፡

4: የ U ቪዛ ጣሪያ ወደ 30 ሺህ እንዲጨምር እንዲያድግ፡፡

3.5 የዩናይትድ ሴቴትስ ወታደሮችን በማገዝ ሂደት ውስጥ ለሚሳተፉ የውጪ አገር ዜጎች ተጨማሪ ጥበቃዎች እንዲደረግ፡፡

4/ የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤቶችን በተመለከተ

 1.     የቤተሰብ ጉዳዮች በአንድ ላይ ማስተናገድ እንዲሰፋ
 2.     የተከማቹ እና ውዝፍ ጉዳዮች በፍጥነት እንዲስተናገዱ
 3.     ለኢሚግሬሽን ዳኞች ተጨማሪ ስልጠናዎች እንዲሰጡ
 4. ዳኞች እና የስደተኞች ጉዳዮችን የሚወስኑ ሰራተኞች ይገባቸዋል ብለው ለሚያምኑባቸው ማመልከቻዎች እፎይታ (relief) እንዲሰጡ ተጨማሪ መብት እንዲሰጥ፡፡
 5.     ለህፃናት፣ ለጥቃት ተጋላጭ ሰዎቸ እና ሌሎችም የህግ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና አስፈላጊው የህግ ባለሙያ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ፡፡
 6.     ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ልጆችን ለሚያስተምሩ የትምህርት ቤት ዲስትሪክቶች አስፈላጊው የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ፡፡

5/ በስራ ቅጥር ስለሚገኙ ቪዛዎች

 1.     ውዝፍ ጉዳዮችን እና የተራዘመ የጥበቃ ጊዜዎች እንዲቃለሉ እንዲደረግ፡፡ እንዲሁ በሃገራት ላይ የተጣሉ የቪዛ መጠን ጣሪያዎች እንዲነሱ እንዲደረግ፡፡
 2.     በ H1B ቪዛ ተቀፅላ ሆነው ወደ ሃገር ውስጥ ለሚገቡ የትዳር አጋሮች የስራ ፍቃድ እንዲያገኙ እንዲደረግ፡፡ እንዲሁም ልጆቻቸው በማመልከት ሂደት ውስጥ ወሳኝ የሆኑ የእድሜ ገደቦች ተፈፃሚነት እንዳይኖራቸው እንዲደረግ፡፡
 3.     ከቀጣሪዎች የሰራተኛ ማህበራት እና የሲቪል መብት ተሟጋቾች ድርጅቶች የተውጣጣ ኮሚሽን የስራ ቅጥር ማረጋገጫ ሂደቶች ላይ አስፈላጊ የሆኑ ማሻሻያዎችን እንዲያቀርብ፡፡
 4.     ጠንከር ያሉ የአሰሪ እና የሰራተኛ ህግ ጥሰቶች ለሚፈፀምባቸው እና ጥሰት ፈፃሚዎቹን ወደ ህግ በማቅረብ ሂደት ውስጥ ከመንግስት አካላት ጋር ለመተባበር ፍቃደኛ የሆኑ ሰዎች የ U ቪዛ ጥበቃ እንዲደረግ፡፡

6/ የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ 

 1. ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ሰፋፊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ፡፡
 2. በድንበር መተላለፊያዎች ላይ የጥገኝነት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ተጨማሪ የገንዘብ እገዛዎች እንዲደረግና ስርዓታዊና ቅልጥፍና በተሟላበት ሁኔታ ጉዳዩ እንዲተገበር፡፡
 3. የመንግስት ኤጀንቶችን እና ኦፊሰሮች ተከታታይ የስራ ላይ ስልጠና እና የስነምግባር ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲዘጋጅ፡፡
 4. በድንበር አካባቢ የሚገኙ ባለድርሻዎች አማካሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም፡፡
 5. የስነ ምግባር ጉድለቶችን የሚያጣሩ ተጨማሪ መርማሪ ኤጀንቶች እንዲዘጋጅ፡፡
 6. DHS (የሃገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት) ያለው ለድንበር አካባቢ አጥሮች እና ለድንበር መከለያዎች ሲባል የስቴት እና የአካባቢ ጥበቃ ህጎችን እና የፌደራል ደንቦችን የመገደብ ስልጣን እንዲከለስ፡፡
 7. ከ DHS (የሃገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት) እና HHS (የጤና እና ሰው ሃብት ልማት መስሪያ ቤት) እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተውጣጡ ባለሙያዎች በድንበር እና ቀረጥ ጥበቃ ባለስልጣን (CBP) ተይዘው የሚቆዩ ግለሰቦች የቤተሰብ አባላት እና ግለሰቦች አያያዝን በተመለከተ የሚተነትን መመሪያ እንዲዘጋጅ፡፡
 8. ስደተኞችን መጠቀሚያ የሚያያርጉ ህገወጥ የሰወች ዝውውር ወንጀለኞችን በሰፊው ለመቅጣት የሚያስችል አቅም እንዲገነባ፡፡ እንዲሁም በመካከለኘው አሜሪካ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖችን ለመከላከል የተቋቋሙ ግብረ ሃይሎች በጠንካራ መልኩ እንዲደራጁ እንዲደረግ፡፡
 9. ለኤልሳልቫዶር፣ ጓቲማላ እና ሁንዱራስ የሚደረጉ ድጋፎች እንዲጨመሩ እንዲደረግ፡፡
 10. በመላው የመካከለኛው አሜሪካ አካባቢ የሚገኙ ስደተኞችን እና ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ለማስፈር እና ለማቋቋም የሚረዱ የምዝገባ ጣቢያዎች ለዚህ ስራ ብቻ እንዲያገለግሉ ሆነው እንዲቋቋሙ፡፡
 11. ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናትን በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋር ለማገናኘት በስራ ላይ የነበረ ፕሮግራም ተመልሶ ተግባራዊ እንዲሆን፡፡

ማስታወሻ፡- በዚህ ፐሮግራም መቋረጥ ምክንያት የተከሰተው የህፃናት ልጆች ከቤተሰቦቻቸው የመለያየት ችግር በጣም አሳፋሪ ከሚባሉ ክስተቶች ውስጥ አንዱ ነበር፡ የሚታወስ የቅርብ ቀን ትውስታ ነው፡፡

 

 1. በመካከለኛው አሜሪካ የሚኖሩ እና የተፈቀደ ስፖንሰርሺፕ(Sponsorship) ማመልከቻ ያላቸው የቤተሰብ አባላት በፍጥነት መቀላቀል እንዲችሉ የሚያመቻች ጊዜያዊ ፕሮግራም እንዲቋቋም፡፡

ለማጠቃለል ያህል እንደ ወትሮው ትህትና የተሞላው የላቀ የስራ ባህላችንን ከ25 ዓመታት በላይ ካደረግነው በበለጠ አጠናክረን እንደምንቀጥል ስንገልፅላችሁ ከታላቅ አክብሮት ጋር ነው፡፡

 

የከበረ ሰላምታ ከሁልጊዜ አገልጋዮቻችሁ

 

 

የሚ ጌታቸው ኢሚግሬሽን ህግ ቢሮ ጠበቆች እና የስራ ባልደረቦች፡፡

Available 24/7
408-292-7995

Get Help Today

Our team of experienced immigration attorneys are ready to answer your questions.

"*" indicates required fields

This field is for validation purposes and should be left unchanged.